Jeremiah 30

የእስራኤል ሕዝብ መመለስ

1 ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፤ 2“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የነገርሁህን ቃል ሁሉ በመጽሐፍ ጻፈው። 3እነሆ፣ ሕዝቤን እስራኤልንና ይሁዳን’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር የምመልስበት ጊዜ ተቃርቧል፤
ወይም የሕዝቤን የእስራኤልንና የይሁዳን ዕድል ፈንታ እመልሳለሁ
እነርሱም ይወርሷታል’ ይላል እግዚአብሔር።”

4 እግዚአብሔር ስለ እስራኤልና ስለ ይሁዳ የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ 5እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ ‘የፍርሀትና የሽብር ጩኸት ተሰምቷል፤
ሰላምም የለም።
6እስቲ ጠይቁ፤ ተመልከቱም፤
ወንድ መውለድ ይችላል?
ታዲያ ወንድ ሁሉ ምጥ እንደ ያዛት ሴት፣
እጁን በሆዱ ላይ አድርጎ፣
የሰውስ ሁሉ ፊት ጠቍሮ የማየው ለምንድን ነው?
7ያ ቀን ምንኛ አስጨናቂ ይሆናል!
እንደዚያም ያለ አይኖርም፤
ለያዕቆብ የመከራ ጊዜ ነው፤
ነገር ግን ይተርፋል።

8“ ‘በዚያን ቀን’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር
‘በጫንቃቸው ላይ ያለውን ቀንበር እሰብራለሁ፤
እስራታቸውንም እበጥሳለሁ፤
ከእንግዲህ ባዕዳን አይገዟቸውም።
9ነገር ግን ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር
ለማስነሣላቸውም ለንጉሣቸው፣
ለዳዊት ይገዛሉ።

10“ ‘ስለዚህ፤ አገልጋዬ ያዕቆብ ሆይ፤ አትፍራ፤
እስራኤል ሆይ፤ አትደንግጥ፤’
ይላል እግዚአብሔር
‘አንተን ከሩቅ አገር፣
ዘርህንም ከተማረኩበት ምድር እታደጋለሁ፤
ያዕቆብ ተመልሶ በሰላምና በርጋታ ይቀመጣል፤
የሚያስፈራውም አይኖርም።
11እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፤ አድንሃለሁም’
ይላል እግዚአብሔር
‘በአሕዛብ መካከል በትኜሃለሁ፤
እነዚህን አሕዛብ ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁ፤
አንተን ግን ሙሉ በሙሉ አላጠፋህም፤
በመጠኑ እቀጣሃለሁ እንጂ፣
ያለ ቅጣት አልተውህም።’
12እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ ‘ስብራትህ የማይጠገን፣
ቍስልህም የማይድን ነው።
13የሚሟገትልህ ሰው የለም፤
ለቍስልህ መድኃኒት አይኖርም፤
ፈውስም አታገኝም።
14ወዳጆችህ ሁሉ ረስተውሃል፤
ስለ አንተም ግድ የላቸውም።
ጠላት እንደሚመታ መታሁህ፤
እንደ ጨካኝም ቀጣሁህ፤
በደልህ ታላቅ፣
ኀጢአትህም ብዙ ነውና።
15ፈውስ ለማይገኝለት ሕመምህ፣
ስለ ቍስልህ ለምን ትጮኻለህ?
በደልህ ታላቅ፣ ኀጢአትህም ብዙ ስለሆነ፣
እነዚህን ሁሉ አድርጌብሃለሁና።

16“ ‘ነገር ግን አሟጥጠው የበሉህ ሁሉ እንደዚያው ይበላሉ፤
ጠላቶችህ ሁሉ ለምርኮ ዐልፈው ይሰጣሉ፤
የሚዘርፉህ ይዘረፋሉ፤
የሚበዘብዙህም ሁሉ ይበዘበዛሉ።
17አንተን ግን መልሼ ጤነኛ አደርግሃለሁ፤
ቍስልህንም እፈውሳለሁ፤’
ይላል እግዚአብሔር
‘የተናቀች፣
ማንም የማይፈልጋት ጽዮን’ ብለውሃልና።
18እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ ‘እነሆ የያዕቆብን ድንኳን ምርኮ እመልሳለሁ፤
ለማደሪያውም እራራለሁ፤
ከተማዪቱ በፍርስራሿ ጕብታ ላይ ትሠራለች፤
ቤተ መንግሥቱም በቀድሞ ቦታው ይቆማል።
19ከእነርሱም የምስጋና መዝሙር፣
የእልልታ ድምፅ ይሰማል።
እኔ አበዛቸዋለሁ፤
ቍጥራቸውም አይቀንስም፣
አከብራቸዋለሁ፤
የተናቁም አይሆኑም።
20ልጆቻቸው እንደ ቀድሞው ይሆናሉ፤
ማኅበረ ሰቡም በፊቴ የጸና ይሆናል፤
የሚጨቍኗቸውን ሁሉ እቀጣለሁ።
21መሪያቸው ከራሳቸው ወገን ይሆናል፤
ገዣቸውም ከመካከላቸው ይነሣል፤
ወደ እኔ አቀርበዋለሁ፤ እርሱም ይቀርበኛል፤
አለዚያማ ደፍሮ፣
ወደ እኔ የሚቀርብ ማን ነው?’ ይላል እግዚአብሔር
22‘ስለዚህ እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፤
እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ።’ ”

23እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማዕበል፣
በቍጣ ይነሣል፤
የሚገለባብጥም ዐውሎ ነፋስ፣
በክፉዎች ዐናት ላይ ይወርዳል።
24የልቡን ሐሳብ ሳይፈጽም፣
የእግዚአብሔር ቍጣ፣
እንዲሁ አይመለስም፤
በሚመጡትም ዘመናት፣
ይህን ታስተውላላችሁ።
Copyright information for AmhNASV